2 Chronicles 6

1ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ 2እኔም አንተ ለዘላለም ትኖርበት ዘንድ፣ ይህን ታላቅና ድንቅ ቤተ መቅደስ ሠራሁልህ።”

3መላው የእስራኤል ጉባኤ እዚያው ቆመው ሳሉ፣ ንጉሡ ዘወር ብሎ ባረካቸው። 4እንዲህም አለ፤

“ለአባቴ ለዳዊት በቃሉ የሰጠውን ተስፋ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እንዲህ ብሏልና፤
5‘ሕዝቤን ከግብፅ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ይሠራበት ዘንድ ከማናቸውም የእስራኤል ነገድ ከተሞች አንድም አልመረጥሁም፤ ወይም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም። 6አሁን ግን ስሜ በዚያ እንዲሆን ኢየሩሳሌምን፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲገዛም ዳዊትን መርጫለሁ።’

7“አባቴ ዳዊት፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር፤ 8እግዚአብሔር ግን፣ ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ አስበህ ነበር፤ ይህን በልብህ በማሰብህ መልካም አድርገሃል፤ 9ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’

10እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሟል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። 11በዚያም እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ኪዳን ያለበትን ታቦት አኑሬአለሁ።”

ሰሎሞን በምረቃው ጊዜ ያቀረበው ጸሎት

6፥12-40 ተጓ ምብ – 1ነገ 8፥22-53 6፥41-42 ተጓ ምብ – መዝ 132፥8-10 12ከዚህ በኋላ ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባሉበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ። 13ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፣
2.3 ሜትር ይህል ነው።
ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ
1.3 ሜትር ይህል ነው።
የሆነ የናስ መድረክ በውጭው አደባባይ መካከል አሠርቶ ነበር፤ በመድረኩም ላይ ወጥቶ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤
14እንዲህም አለ፤

“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋር የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤
15ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው።

16“አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ከቶ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት። 17እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም።

18“በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! 19ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ። 20ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ በቀንም በሌሊትም የተገለጡ ይሁኑ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ። 21ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልዩበትም ጊዜ ልመናቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ከሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።

22“አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ 23ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም። በደለኛውን፣ በደሉን በራሱ ላይ አድርገህ እንደ ሥራው በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ። ንጹሑም በደለኛ አለመሆኑን አስታውቅ፤ እንደ ንጽሕናውም ክፈለው።

24“ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፣ ወደ አንተ ተመልሰውም በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ በመጸለይና ልመናቸውን በማቅረብ ስምህን ቢጠሩ፣ 25በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው።

26“ሕዝብህ አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ባይዘንብ፣ አንተ ስለ አስጨነቅሃቸው ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፣ ስምህን ቢጠሩና ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣ 27በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚኖሩበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ በሰጠኸውም ምድር ላይ ዝናብን ላክ።

28“በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚወርድባት ጊዜ፣ ወይም ደግሞ በየትኛውም ከተማቸው ሳሉ ጠላት በሚከብባቸው ጊዜ፣ ወይም ማናቸውም አደጋ ወይም ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ 29ከሕዝብህ ከእስራኤል ማንም ሰው ጭንቀቱና ሕመሙ ተሰምቶት፣ እጁን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ፣ 30በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ ይቅርም በል፤ የሰውን ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ፣ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ክፈለው፤ 31ይህም ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ አንተን እንዲፈሩህና በመንገዶችህ እንዲሄዱ ነው።

32“ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ ባዕድ ሰው ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ኀያሉ እጅህና ስለ ተዘረጋው ክንድህ ሰምቶ ከሩቅ አገር በመምጣት ወደዚህ ቤተ መቅደስ በሚጸልይበት ጊዜ፣ 33በሰማይ በማደሪያህ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።

34“ሕዝብህ አንተ በምትልካቸው ቦታ ሁሉ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ፣ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩ፣ 35ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ የጠየቁህንም አድርግላቸው።

36“መቼም የማይበድል ሰው የለምና፣ አንተን በበደሉህ ጊዜ፣ ተቈጥተሃቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር በምርኮ ለሚወስዳቸው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ 37በተማረኩበት አገር ሆነው የልብ ጸጸት ተሰምቷቸው ንስሓ ቢገቡና በምርኮ ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ቢሉ፣ 38ተማርከው በሚኖሩበትም ምድር ሆነው በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹምም ነፍሳቸው ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣ 39ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ በማደሪያህ ስማ፤ የጠየቍህንም አድርግላቸው። የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል።

40“አሁንም አምላኬ ሆይ፤ በዚህ ስፍራ ወደ ቀረበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፣ ጆሮዎችህም የሚያደምጡ ይሁኑ።

41“አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ ተነሥ፣
ከኀይልህ ታቦት ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ ግባ።
እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ካህናትህ ድነትን ይልበሱ፤
ቅዱሳንህም በቸርነትህ ደስ ይበላቸው።
42 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ የቀባኸውን አትተወው፤
ለባሪያህ ለዳዊት ቃል የገባህለትን ጽኑ ፍቅር ዐስብ።”
Copyright information for AmhNASV